በመጀመሪያ በእድሜያችን ላይ ዘመን ጨምሮ ያሻገረን ጌታ ስሙ ለዘለዓለም እስከ ለዘለዓለም የተባረከ ይሁን !!
ሁሌ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር በዘመኑ ሩጫ እየተደነቅን ውስጣችንን የሚኮረኩረን ሀሳብ በተፈጸመው አመት..ምን ሰራሁ ከህልሜስ ምን አሳካሁ ? የሚል ነገር ልናውጠነጥን እንችላለን። በቀኑ እንኳን ያቀድንወን ከግብ አለማድረሳችንን ስናስብ የቅሬታ ስሜትን ይፈጥራል። ታድያ ለስኬታችን ትልቁን አስተዋፅኦ የሚያደርገው ጊዜን የመጠቀም ስልታችን ከሆነ እስቲ በዛ ዙሪያ አንድ ሁለት እንበል ።
ጊዜን እንዴት ነው የምንገልጸው ?
ጊዜ እግዚአብሔር ከሰጠን ስጦታዎች ትልቁ ስጦታ፤ በምንም ዋጋ ሊተመን የማይችል አንዴ ካለፈ ተመልሶ የማይገኝና የማይተካ ውድ ሸቀጥ ነው።
"ጊዜ ወርቅ ነው ይባላል። " እንደኔ አመለካከት ግን በገበያ ዋጋ ከፍና ዝቅ ሊል የሚችል በሰው እጅ የሚሰራ ሲሆን ጊዜ ግን በእግዚአብሔር ቃል የተፈጠረ ነውና ከወርቅ ጋር ንፅፅሩ አያረካኝም።
ጊዜን በምንም ዋጋ ልንተምነው አንችልም። በነፃ የተሰጠ ስለሆነ መሸጥም መለውጥም አይቻልም።
አንዳንድ እቃዎች በቆዩ ቁጥር ዋጋቸው ( depreciate) እንደሚቀንሰው ሁሉ ጊዜም እያጠረ እንጂ እየጨመረ አይሄድም።
በምድር ላይ ያለው ቆይታችን በእግዚአብሔር የተወሰነ ነው ከዛ አይጨምርም አይቀንስም። ደግሞም እግዚአብሔር በአላማ እንደፈጠረን ሲገባንና የግባችንንሞ መዳረሻ ስናውቅ ለጊዜ ጠንቃቃ እንሆናለን።
ለሰው ልጅ ከሞት የበለጠ አሳዛኝ ነገር አለማ የለሽ ህይወት መኖር ነው ይባላል።
እግዚአብሔር ያለማዳላት ለሁላችንም 24 ሰአት ሰጥቶናል።
የምንኖርለትና የምንሞትለት ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ አላማ መር የሆነ ህይወት እንድንኖር ብሎም ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም ይረዳናል።
በዚህ ዘመን የምንኖር ሰዎች ጊዚያችንን ብዙ የሚይዝብንነገር አለ ግን ዋናውና አንገብጋቢው ጥያቄ ፍሬያማ ሆነናል ወይ የሚለው ነው። ሰው ሰአቱ ተጣቦበት ግን ፍሬያማ ላይሆን ይችላል።
ውጤታማ የሚያደርገን ጊዚያችንን ልንሰጠው የሚገባንንና ወደግባችን ለመድረስ የሚጠቅመንን ነገር ለይተን ስናውቅ ብቻ ነው። አለበለዚያ ከንቱ ሩጫ ወይም ድካም ይሆናል።
በየእለቱ ለቀኑ የሚሆን እቅድ ካላወጣን ጊዚያችን በዋል ፈሰስ ያልፋል።
ታዲያ ይሄን ያህል ስለጊዜ ጠቃሚነት ካወራን ጊዚያችንን እንዴት እንጠቀም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ትንሽ መሰረታዊ የሆነና በዚህ ዙሪያ ሊረዳን የሚችል ነጥቦችን በትንሹ እንዳስ።
1. "First thing is first " ይላሉ ነጮቹ ...በመጀመሪያ ቀናችንን በፀሎት መጀመር ማለትም የቀናችንን በኩራት ለጌታ ስንሰጥ የቀረውን ሰአት ጌታ ይባርከዋል።
2.በጠዋት መነሳት የነቃ ወይም ያልተበረዘ አእምሮ ስለሚኖረን በጥቂት ሰአት ብዙ መስራት እንድንችል ይረዳናል።
3. ለየቀኑ የምንሰራውን ነገር በዝርዝር መጻፍ ዝም ብሎ ከመዋለል ያድነናል።
4. እንደየአስፈላጊነቱ ቅደም ተከተል ማስያዝ ጠቃሚነቱ ጊዜ ቢያጥረን እንኳን የግድ መሰራት ያለበትን ነገር በሰአቱ እንዲሰራ ሁኔታን ያመቻችልናል።
5. ረጅም ጊዜ የሚወስደውን በመጀመሪያ ማድረግ የሚረዳን አዕምሯችን ወይም ጉልበታችን ሳይደክም በፊት ብዙ ጊዜ የሚፈልገውን ነገር እንድናከናውን ያግዘናል።
6. በየጊዜው የሰአት አጠቃቀማችንን ክለሳ በማድረግ ሰአታችንን በከንቱ የሚወስድብንን ማንኛውም ነገር ማስወገድ..,ወዘተ..
መጥፎ ልማድ እንዳለ ሁሉ መልካም የሆነውን ልማድ ማጎልበት ይቻላል።
አግባብ ያለው የጊዜ አጠቃቀምን ለመለማመድ ውሳኔና በውሳኔ መፅናትን ይጠይቃል። እኛ የራሳችንን ድርሻ ስናደርግ መንፈስ ቅዱስም ይረዳናል።
ያለእኔ ምንም ማድረግ አትችሉም ያለን ጌታ በሁሉም የሕይወታችን ዘርፍና እንቅስቃሴ ውስጥ ነው።
ጊዜ ማለት ምን እንደሆነና ለጊዜ አጠቃቀማ የሚጠቅሙንን ነጥቦች በጥቂቱ ካየን ትንሽ ደግሞ እንቅፋት የሚሆኑትን ነገሮች ለማየት እንሞክር።
ትንቢተ ኢሳይያስ 43:18 -19፤
የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ።
እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለህ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ።
ቃሉም እዚህ ላይ እንደሚያሳስበን የሗላን ማሰብ ወደፊት ለመሄድ ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ነው ። ይህን ሀሳብ በሁለት አቅጣጫ ማየት እንችላለን።
አንዱ ባለፈው የሰራናቸውን ስህተቶች በማሰብ ተምረንበት ወደፊት ከመሄድ ይልቅ በፀፀት ጊዜን ማባከን በሌላ በኩል ደግሞ የተከናወነልንን ነገር በማሰብ በእርካታ በመቀመጥ ወደ ፊት ገና ያልያዝንውን ነገር እንዳንጨብጥ ያዘናጋል።
ወጣት እያለን ብዙ ነገር በትኩስ ጉልበት መስራት ስንችል በወቅቱ ጊዜን ካልተጠቀምንበት ግን አቅም ጉልበት ፍጥነት እየደከመ ወይም እየከዳ ስለሚሄድ ብዙ ያታግለናል ብሎም ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል።
አንድ ሰው ሲናገር እንዲህ አለ ፣
"እግዚአብሔር ዘመናችንን የሚለካው በቁጥሩ ማነስና መብዛት ሳይሆን በተሰጠን እድሜ ምን ያህል ለተሰጠን አላማ በምድር ቆይታችን አስተዋፅኦ ባደረግንበት ነው።”
ይሄን ሀሳብ ለማስረዳትም የሰጠው ምሳሌ ማቱሳላ 969 አመት ኖሮ ሞተ። በዛ ጊዜ ውስጥ የሰራው ነገር ግን አልተገለፀም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ 30-33 አመት አካባቢ ነው በምድር ላይ የኖረው ግን እግዚአብሔር በሱ ላይ ያለውን አላማ በሙሉ ፈፅሞ ነው የሄደው። የመጨረሻም ቃሉ "ተፈፀመ" የሚል ነበር።
እኛም የኖርንበት የእድሜ ርዝመት ሳይሆን ጌታ በሰጠን እድሜ ምን ያህል ተጠቅመንበታል ነው ዋናው ቁምነገር።
“ Better late than never ."ይላሉ። ግን ከዚህ ልምምድ ወጥቶ ነገርን በሰአቱ ማድረግ መልካም ውሳኔ ነው።
እግዚአብሔር ከዘመን ዘመን የሚያሻግረን በውስጣችን ያለውን ፀጋ እንድንጠቀምበት ጊዜን ሊሰጠን ስለወደደ ነው። አንድ አስተማሪ ያለው ነገር ትዝ አለኝ። "ብዙ ሰው እግዚአብሔር በውስጡ ያስቀመጠውን ፀጋ ሳይጠቀም በመሄዱ የዛ ሰው ስጦታ በምድር እያለ ሌሎችን መርዳት ሲገባው የመቃብር ሲሳይ ሆኖ ይቀራል አለ። "
ሁላችንም ራሳችንን እንድንመረምር ያስፈልጋል። እግዚአብሔር በውስጣችን ያስቀመጠውን ፀጋ ምን ያህል እያገለገልንበት ነው ??
ስኬት ከመፅሐፍ ቅዱስ አንፃር ስናየው እግዚአብሔርን በመታዘዝ በመንፈስ ቅዱስ ሀይል በእግዚአብሔር ፍቅር ለእግዚአብሔር መንግሥት በህይወት እስካለን ድረስ በተሰጠን ውስን ጊዜ ሰርቶ ማለፍ ነው።
ታዲያ ወደ 2024 ስንሸጋገር ባለፈው አመት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ መከናወን በሆነልን ነገር ላይ አባታችንን አመስግነን ያልፈፀምናቸውን ነገሮች ደግሞ ለመፈፀም የምናቅድበትና ብሎም ተግባራዊ የምናደርግበት በአዲስ ጉልበትና ሀይል የምንዘረጋበት ህልማችንን እውን የሚሆንበት ዘመን እንዲሆንልን እግዚአብሔር ሁላችንንም ይርዳን !!